“ደስ ሲል!”
ፊቱ ቅጭም ብሎ አንገቱን ደፍቶ በቀስታ ከአዳራሹ ወጣ:: የለመደው አዳራሽ ስለሆነ ብቻ እግሩን እያነሳ እይጥለዋል እንጅ ወዴት እንደሚሄድ እንዴት እንደሚራመድ አያውቀውም:: ዳዊት ከአዳራሹ ከወጣ በኋላ ዘወር ሲል አይኑን ከባነሩ ጋር አፈጠጠና “ኦርቶዶድሳዊ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን አስተምሮዋን እንጠንቅቅ፣ ድርሻችንን እንወቅ” የሚለውን አነበበና ፍርጥም አለ:: ዳዊት ከቤተ ክርስቲያን መልስ ቁርሱን ከበላ በኋላ ማህበረ ቅዱሳን ኮምቦልቻ ወረዳ ማዕከል ያዘጋጀውን 5ኛውን ልዩ አውደሪ ለማየት ትኬቱን ቆርጦ ሲገባ ባነሩን እንዴት እንዳላስተዋለው ገረመው:: “መልዕክቱኮ ከባነሩ አለ” አለ ለራሱ:: ትንሽ እንደተጓዘ ከፅዱ ስር ቁጭ አለ:: ድንገት ጓደኛው መለሰ ከፊቱ ቆሞ “ዳዊት ምን ሆነሃል? ፈዘሃል እኮ!” አለው:: ዳዊትም “አውደሪው እንዴት ነበር?” አለው ለስለስ ባለ ድምፅ:: መለሰም “ደስ ይላል! አንተ! አቅራቢዎችን አየሃቸው? አቤት ብቃት! አለባብሳቸው ሲያምር አንተ! ደግሞ እኮ አይሳሳቱም! ኧረ በስመ አብ! ደስ ይላል!” አለው:: ዳዊትም በመገረምና በመናደድ ስሜት ትኩር ብሎ ይመለከተው ነበር:: ዳዊትም ከፊቱ የቆመውን መለሰን ከቁብ ሳይቆጥር በሀሳብ ደመና ተጭኖ መብረር ጀመረ:: “ለካስ እስከ ዛሬ ስህተት ነበርኩ! ለምን ፓትሪያሪኩ ይህን አያደርጉም? ጳጳሱ የት ሄደው ነው? መምህሩስ? ሰበካ ጉባኤው ምን እየሰራ ነው? የግቢ ጉባኤ ስራ አስፈፃሚዎች ምን ሆኑ? ወዘተ ........ ያልሁት ለካስ ስህተት ነበርኩ! ደግሞስ ማሰብ ስራ መስሎኝ እራሴን ሳታልል መኖሬ! ለመሆኑ የኔን ድርሻን እንዴት አላወቅሁም?” እያለ እራሱን ጠየቀ:: ከዚያም የጓደኛው መልስ ደነቀውና “‘ደስ ይላል!’ ይለኛል እንዴ? እኔ የሚገርመኝ አውደሪው የተዘጋጀው ደስ እንዲለን ነው እንዴ? ወይስ አውደሪው ውስጥ የገባነው ሰው ልናይ ነው? ነውስ አለባብሳቸውን ልንመለከት? ግርም የሚለኝ.... አንድ ነገር ሲሰራ ወይም ሲዘጋጅ የራሱ የሆነ አላማ አለው:: እኛ ግን አላማውን ረስተን ሌላ አዲስ አላማ እንፈጥለታለን:: መክቱበት ተብለን ጋሻ ስንሰጥ የአመድ ማፈሻ እናደርገዋለን! ተዋጉበት ተብለን ጦር ስንሰጥ የእጥር ማገር እናደርገዋለን! መረጃ ተለዋወጡበት ተብለን ፌስቡክ ብንሰጥ እኛ ግን ዘረኝነትን ማስፋፊያ፣ በስድብ መራከሻ፣ የዝሙት ማስፋፊያ፣ ጦርነት ማወጃ፣የሌላውን እምነት መንቀፊያ አደረግነው:: ደግሞስ መመልከት ያለብን አውደሪውን ወይስ አቅራቢዎችን? ወይ እኛ? ስብከቱን ሳይሆን ሰባኪውን እንመለከታለን! ትምርቱን ሳይሆን መምህሩን እንመለከታለን! ምዕመኑን ሳይሆን ገንዘቡን እንመለከታለን! የህዝቡን ጥያቄ ሳይሆን ስልጣኑን እንመለከታለን! ስራውን ሳይሆን ደምወዙን እንመለከታለን! ስልጠናውን ሳይሆን ውሎዓበሉን እንመለከታለን! ቅዳሴውን ሳይሆን ቀዳሹን እንመለከታለን! መዝሙሩን ሳይሆን ዘማሪውን እንመለከታለን! ሰብዕናን ሳይሆን ደምግባትን እንመለከታለን! ሰውነቱና ሳይሆን የኑሮ ደረጃውን እንመለከታለን! ፅሑፉን ሳይሆን ፀሐፊውን እንመለከታለን! በምእመኑ ገንዘብ ምን ዓይነት ህንፃ እንስራ እንጅ ስንት ሰው ለስጋወ ደሙ እናብቃ አንልም፣ እኛ የቤተ ክርስቲያን መሆን ሲገባን ቤተ ክርስቲያንን የራሳችን ለማድረግ እንፈልጋለን፣ እኛ ወደ ስርዓቱና ህጉ መሄድ ሲገባን ስርዓቱን ወደ እኛ ለማምጣት እንፈልጋለን፣ መሪ መሆን ሲገባን ገዥ እንሆናለን:: ወይ ስሜትን ብቻ ማዳመጥ? ኧረ ለመሆኑ ልቦናችን የት ሄደ? በላይ ዘለቀ ሆይ ስትሰቀል “አንች ሀገር ወንድ አይብቀልብሽ!” ነው ብለህ የተራገምህ ወይስ “አንች ሀገር ልብ ያለው ሰው አይብቀልብሽ!” ያለሃት?እኔ ግን ሁለተኛው ይመስለኛል! እርግማኑ እኮ በኛ ደረሰ፡፡ ለነገሩ ሁለቱም ነው ጀግናስ ወንድ የትአለና ዘራፍ! ብሎ ለሀገሩ የሚነሳ? ወይ ዘመን! ምኑ ላይ ደረስን!” እያለ በሃሳብ ሲከንፍ ድንገት ስልኩ ጠራ:: ድብዝዝ ባለ ስሜት አካባቢውን ቃኘው ምንም ሰው የለም:: መለሰም ሲያናግረው ስላልመለሰለት ትቶት ሄዷል:: ዳዊት ፍርጥም ብሎ ከተቀመጠበት ተናሳና ጉዞውን ጀመረ ልቡ ግን አውደሪው ላይ:-ትዕይንት-4 ላይ ቀርቶ ነበር:: ድርሻውን ፍለጋ የራሱን የመሰረት ድንጋይ ለቤተክርስቲያን ሊያስቀምጥ ልቡ አውደሪው ላይ ቀርቶ ነበር:: .... ....... ....... ...... ....... ............... ................ ................... ............. ....... ............... ....... by M.T
Comments
Post a Comment