አካባቢው በጫጫታና በሁከት ተሞልቷል :: ሁሉም መናገራቸውን እንጅ ምን እንደሚናገሩ፣ምን እንደሚነገር፣ ማን እንደሚናገር አያዳምጡም :: ብቻ አፋቸው ያመጣውን፣ ስሜታቸው የሚያዝዛቸውን ይናገራሉ :: ስሜታችው እየጋለ ወደ ድብድብ ሊያመራ ይመስላል :: ሁሉም የኔ ነው ትክክል ! የኔ ነው ትክክል ! በሚል ስሜት ተውጠው የሌላው ሀሳብ አይጥመውም፥ አያዳምጠውምም :: ከመካከላቸው አንዱ “ ይህ እኮ “ ብር ” ነው ምን ነካችሁ ? ይህ እኮ ጫማ፣ ልብስ፣ቲማቲም፣ሽንኩርት የምንገዛበት ብር እኮ ነው ” ይላል :: አንዱ ደግሞ ፀጉሩን እየፈተለ በአንድ እጁ ሱሪውን ይዞ “ ኧረ ሸ ነው ምን ሆናችኋል ? ይህ እኮ ” ጨላ “ ነው ! ቀፍላችሁ አታውቁም እንዴ ?” ይላል :: ሌላው ደግሞ በሲጋራና በጫት የበለዙ ጥርሶቹን እያሳየ “ ኧረ ፍሬንድ አምፖላችሁ ላላ እንዴ ? ይህ እኮ ” መላ “ ነው ! የበርጫ ምናምን መሸመቻ ነው እኮ ?” ይላል :: አንዱ ሱፍ ይለበሰ ደግሞ “ ወገኖቸ ምን እያላችሁ ነው ? ይህ እኮ ” ገንዘብ “ ነው ! ባንክ አትጠቀሙም እንዴ ? ብትቆጥቡ እኮ ታውቁት ነበር ! ይህ ” ገንዘብ “ ነው !” ይላል :: ከሀሳቡ ይልቅ ምላሱ የሚቀድም ሌላው ደግሞ ” ኧረ ላሽ ይህ ይጠፋችኋል ? ይህ እኮ ” ፍራንክ “ ነው ! ቆይ ከቤተሰብ ፈልጣችሁ አታውቁም እንዴ ?” ይላል :: ሌላው ባለስልጣን የሚመስል ደግሞ ቦርጩን እየገፋ “ አይ ከእውቀት ነፃ መሆን ! ይህ እኮ ” በጀት “ ነው ! ሀገሪቱን እያንቀሳቀሰ ያለው እኮ ይህ ነው ! የተለያዩ መሰረታዊ ...