ፈተናና አወዳደቅ

ፈተናና መውደቅ 
ወደ ክፍል ዘው ብሎ ገብቶ “ምን ዋጋ አለው? ከንቱ ድካምኮ ነው! ከንቱ ድካም!” አለ በጎረነነ ድምፅ ፊቱን እንደ ክረምት ሰማይ አጥቁሮ:: ተማሪዎች ክው ብለው ቀሩ:: በፈተናቸው ፈተና መሆኑ ገብቷቸዋል:: መምህሩ ሁሉንም ተማሪዎች በሚያስፈራ ዓይኑ እየገረመመ “ምን ሁናችሁ ነው? ሳስተምር የት ሄዳችሁ ነበር? የለፋቴ ውጤት የት አለ?” ብሎ ጥያቄውን አዥጎደጎደባቸው:: ተማሪዎች አንገታቸውን ደፍተው የፍራት ስሜት እየታየባቸው መልሳቸውን የሚያዘጋጁ ይመስላሉ:: “እንዴት አንድ የሚሰራልኝ ተማሪ አጣለሁ? መልሱልኛ? ለምን ወደቃችሁ?” ብሎ አፈጠጠባቸው:: ደርብ ቀና ሲል ዓይኑ ከመምህሩ ዓይን ጋር ተጋጨ:: መምህሩም “እ ደርብ እስኪ ንገረኝ ለምን ወደቅህ?” አለው ከንዴቱ ጋብ እያለ:: ደርብም “ያው የታወቀ ነው ቀድሜ አውቄያለሁ እንደማልመልሰው” ብሎት እርፍ አለ:: መምህሩ ንዴቱ ውስቱን እያርመጠመጠው “እሽ መሰረት ምን ሆነሽ ነው የወደቅሽ?” አላት:: መሰረትም ፈራ ተባ እያለች “የጥያቄው ብዛት ሃያ መሆኑን ሳውቅና ፃፉ ሲበዛ እኔ እንደምወድቅ አውቄያለሁ” አለች:: “ጉድኮ ነው! እሽ መለሰ ምን ሆነህ ነው የወደቅኸው?” አለ ዓይኑን መለሰ ላይ ተክሎ ተስፋ በመቁረት ስሜት:: መለሰም ድፍረት በተሞላበት ስሜት “አይ እኔ እንኳ የቻልኩትን ሁሉ ሞካክሬዋለሁ ብወድቅም ከጸጸት ድኛለሁ” አለ:: መምህሩ የተማሪዎች ሁኔታ ገረመው:: ተማሪዎችንና የራሱን አካል ክፍል ውስጥ አስቀምጦ በሀሳብ ፈረስ ጋራው፣ ሸንተረሩ: ዱሩና ተራራው ሳይገድበው ይጋልብ ጀመር:: “ጉድ እኮ ነው ስንት ሰው ነው ያለው? ገና ሳይፈተን ቀድሞ የሚወድቅ፣ እየተፈተነ እዛው የሚወድቅ፣ ተፈትኖ ደግሞ ኋላ የሚወድቅ: ለካ የመውደቅም አወዳደቅ አለው: ያደለው እንደ ቡና ዱቄት[በእሳት ሲፈተን] ፈተና ሲፈተን ከራሱ አልፎ ለሌሎች በተረፈ ካልሆነ እንዴት ሳይፈተን ሰው ይወድቃል? ሰው እንዴት የማለፍን ወኔ ረግጦ የመወደቅን ሀርግ ይጨብታል? ፈተናን ለመጋፈጥ የፈተናን መዋጊያ ዝናር ይታጠቃል እንጂ እንዴት ለመውደቅ እጁን አሳልፎ ይሰጣል? ተፈትኖ እንደ እንቁላል ይጠነክራል እንጂ እንዴት እንደ ድንች በፈተና ሰው ፍርክስክሱ ይወጣል? ሰው መሳሪያውን አቀባብሎ ጠላቱን ይጋፍጣል እንጂ እንዴት የሰራዊቱን ብዛት አይቶ መሳሪያውን ወርውሮ ለመውደቅ ይፈጥናል? ፈተናን ተዋግቶ የተሸነፈ ሰውስ ተስፋ ቆርጦ እጅን ከመስጠት መላን ዘይዶ እራስን ከምርኮ ማውጣት ሲገባ እንዴት ወድቄያለሁ አይቆጨኝም ብሎ ለምርኮ እራሱን ይሰጣል” እያለ የተማሪዎችን አወዳደቅ ሲያወጣ ሲያወርድ በሩ ተንኳኳ:: ከሀሳቡ ብንን ሲል ተማሪዎች ፀጥ ብለው በተደንቆ ያዩታል:: ወደ በሩ ሲመለከት መመህር ቆሞ ሰዓት አልቋል በሚል ምልክት እጁን እየመታ አሳየው:: መምህሩም በሀሳብ ተውጦ ሰዓት እንደጨረሰ ገብቶት ዓይኑን ድቡዝዝ አድርጎ ተማሪዎችን ቃኝቶ ወጣ:: መምህሩ አንገቱን ደፍቶ ““ጉድ እኮ ነው ስንት ሰው ነው ያለው? ገና ሳይፈተን ቀድሞ የሚወድቅ፣ እየተፈተነ እዛው የሚወድቅ፣ ተፈትኖ ደግሞ ኋላ የሚወድቅ: ለካ የመውደቅም አወዳደቅ አለው” እያለ ቢሮ ደረሰ:: 

Comments